የብፁዕ ዶር. አቡነ ገሪማ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ፤ “ጽ/ቤታቸውን ዋልድባቸው ያደረጉ፣ ዓላማ ያላቸው ሥራ ወዳድ ነበሩ”/ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ/ (2023)

የብፁዕ ዶር. አቡነ ገሪማ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ፤ “ጽ/ቤታቸውን ዋልድባቸው ያደረጉ፣ ዓላማ ያላቸው ሥራ ወዳድ ነበሩ”/ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ/ (1)

ሥርዓተ ቀብራቸው፥ ኹለቱ ቅዱሳን ፓትርያርኮች፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህናት፣ ሠራተኞችና ምእመናን፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት በተገኙበት፣ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል

~~~

  • የሥራን ክቡርነት የተረዱ፣ የአገርና የቤተ ክርስቲያን ፍቅር የሚያገብራቸው፣ የየዕለቱን ተግባር ለመሸፈን ድካም የማይበግራቸው፥ ቅን፣ ታዛዥና መላ ሕይወታቸውን በሥራ ያሳለፉ ታላቅ አባት ነበሩ፤
  • የትምህርተ ሃይማኖት፣ የታሪክና የሥርዓት ትውፊቶችን የሚገልጹ ጽሑፎችን በማስረጃ በማቅረብ ለጥናትና ምርምር አድራጊ ሊቃውንት የጎላ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፤ ለቤተ ክርስቲያን ቋሚ ምስክርና ኣርአያ ኾነዋል፤
  • ለኅትመት የሚበቁ በርከት ያሉ ዝግጅቶች አሏቸው፤ ኹለቱ ለንባብ በቅተዋል፤ በ1917 ዓ.ም. ተወልደው፣ ሚያዝያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞተ ዕረፍት ተለይተዋል፡፡

/ዜና ሕይወታቸው/

  • “ቅድስናንና አገልግሎትን አስተባብረው ይዘው በመገኘታቸው ኹሉ ነገር የተፈጸመላቸው ናቸው፡፡ ያቺ ጠባብ ዋሻ ለእያንዳንዱ መነኵሴ ካወቅባት ዋልድባ ናት፡፡ ለብፁዕ አባታችን፣ ጽ/ቤታቸው ዋልድባቸው ናት፤ ዓላማቸውን አላስታጎለችባቸውም፡፡”

/ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ/

  • “በታማኝነት፣ በሐቀኝነት፣ በእውነተኛነት ሥራቸውን አክብረው በሕመም ተይዘው እስካቃታቸው ድረስ ከቢሯቸው አይቀሩም ነበር፡፡ ከብፁዕነታቸው የምንማረው ይህን ነው – ታማኝነት፣ ታዛዥነት፣ ጥብዓት፡፡ ማናቸውንም ዕውቀትና ጉልበት ኹሉ ለቤተ ክርስቲያን ያበረከቱ ትልቅ አባት ነበሩ፡፡”

/ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/

***

ሚያዝያ 30/2011 ዓ.ም.

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜ፡፡
የብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ አጭር የሕይወት ታሪክ

ልደት እና ትምህርት፤

ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የበላይ ሓላፊ፣ በቀድሞ አጠራር በተጉለት እና ቡልጋ አውራጃ ልዩ ስሙ አንፋር ጊዮርጊስ እየተባለ በሚጠራው ቀበሌ፣ ከአባታቸው ከአቶ ወልደ ቂርቆስ አፈሩ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ጽጌ ማርያም ወልደ መድኅን በ1917 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡

በዚኹ በተወለዱበት ቦታ በእናት አባታቸው ቤት በክብካቤ ከአደጉ በኋላ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ፣ አለቃ ገብረ ሕይወት ከተባሉት መምህር ዘንድ ከፊደል እስከ ዳዊት ያለውን የንባብ እና የቃል ትምህርት ተምረዋል፡፡

ፋሺስት ኢጣልያ አገራችን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ወላጅ እናታቸውን ተከትለው ከአንፋር ጊዮርጊስ ወደ እናታቸው አገር ወደ ጋሹ አምባ ካህናተ ሰማይ በመሔድ ከእናታቸው ታላቅ ወንድም ከመምሬ በትረ ወልድ ወልደ መድኅን ዘንድ ለዲቁና የሚያበቃቸውን ትምህርት አጠናቀው ተምረው እንዳበቁ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከግብፃዊው ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ሊቀ ጳጳስ የዲቁናን ሥልጣነ ክህነት ተቀብለዋል፡፡

ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ፣ ወደ አደጉበት አካባቢ ተመልሰው በጋሹ አምባ ካህናተ ሰማይ እና በልዝብ ድንጋይ ቅዱስ ገብርኤል አብያተ ክርስቲያናት በተሰጣቸው የዲቁና ሥልጣነ ክህነት ለተወሰነ ጊዜ ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

የብፁዕ ዶር. አቡነ ገሪማ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ፤ “ጽ/ቤታቸውን ዋልድባቸው ያደረጉ፣ ዓላማ ያላቸው ሥራ ወዳድ ነበሩ”/ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ/ (2)

ከዚህ በኋላ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት አቋቋም ያስተምሩ የነበሩት ታላቅ ወንድማቸው መሪጌታ ዘውዱ ገብረ ወልድ እናታቸውን ለመጠየቅ በመጡበት ወቅት ይዘዋቸው ወደ ጎንደር ጠቅላይ ግዛት ጉዞ አደረጉ፤ የአቋቋም ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንዳሉ የቅኔ ትምህርት መቅደም ያለበት መኾኑን ከወንድማቸው ባገኙት ምክር በመጠቀም ደሴ መድኀኔ ዓለም እና ቦሩ ሜዳ ሥላሴ ከነበሩት መምህራን የቅኔ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

የቅኔውን ትምህርት በበለጠ ለማጠናከር በነበራቸው ፍላጎት መሠረት፣ ወደ ዋድላ ድላንታ ጉዞአቸውን በመቀጠል እንዲሁም በየጁ መርጦ ኢየሱስ ከቅኔው ሊቅ መሪጌታ ገብረ እግዚአብሔር ገበያው ዘንድ ቅኔ ከነአገባቡ ተምረዋል፡፡

ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ፣ በወሎ ክፍለ ሀገር ከነበራቸው የትምህርት ቤት ቆይታ በኋላ በጎንደር በወገራ አይባ ኢየሱስ፣ በባልደርጌ ተክለ ሃይማኖት፣ በደንጎርድባ ጊዮርጊስ እና በዳባት ጊዮርጊስ አብያተ ክርስቲያናት ተመድበው ከሚያስተምሩ መምህራን፣ የቅኔውን ሞያ ከማጠናከር ጋራ ዜማ እና አቋቋም ተምረዋል፡፡ በይቀጥላልም ከጎንደር ጠቅላይ ግዛት ወደ ጎጃም ጠቅላይ ግዛት በማቅናት በዚያ ከሚገኙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በየቦቅላ ቂርቆስ እና በዘብች ኢየሱስ አብያተ ክርስቲያናት ከነበሩት መምህራን ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሸዋ አዲስ አበባ በማምራት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በመዘምርነት ተቀጥረው ማገልገል ጀመሩ፡፡

ከተወሰነ የአገልግሎት ቆይታ በኋላ በኹለተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ መልካም ፈቃድ፣ በ1946 ዓ.ም. በሐረር ልዑል ራስ መኰንን አዳሪ ትምህርት ቤት እና በሐረር መድኀኔ ዓለም ትምህርት ቤት እስከ 10ኛ ክፍል ያለውን ትምህርት አጠናቀዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የዛሬው ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ትምህርት ቤት ገብተው የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡

ተግባር እና አገልግሎት

ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ፣ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ቀደም ሲል ብሥራተ ወንጌል እየተባለ ይጠራ በነበረው ራዲዮ ጣቢያ በዛሬው ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በቀድሞው ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተ ማርያም ወርቅነህ አቅራቢነት፣ በግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ መልካም ፈቃድ የራዲዮ መርሐ ግብር አዘጋጅ በመኾን በ1956 ዓ.ም. ተቀጥረው ማገልገል ጀመሩ፡፡ ብፁዕነታቸው ለኹለት ዓመታት ያህል በራዲዮ ጣቢያ ካገለገሉ በኋላ በሩማንያ ቡካሬስት በተገኘው የስኮላርሽፕ ዕድል ተጠቃሚ መኾን ይችሉ ዘንድ ከተመረጡት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አንዱን ኾነው በቡካሬስት ዩኒቨርስቲ ለ10 ዓመታት ያህል ትምህርተ ሃይማኖት ተምረው በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡

የብፁዕ ዶር. አቡነ ገሪማ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ፤ “ጽ/ቤታቸውን ዋልድባቸው ያደረጉ፣ ዓላማ ያላቸው ሥራ ወዳድ ነበሩ”/ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ/ (3)

ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ፣ የውጭ አገር ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ኹለተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ አመራር ሰጭነት፤

  1. በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ ሓላፊ ኾነው ሠርተዋል፤
  2. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ምክትል አስተዳዳሪ እና ዋና ጸሐፊ በመኾን እየሠሩ እያለ በታላቁ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ማዕርገ ምንኵስናን እንዲሁም በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ማዕርገ ቅስናንና ቁምስናን በተከታታይ ተቀብለዋል፤ በተቀበሉት ሥልጣን በመሥራት ላይ እንዳሉ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሐምሌ 9 ቀን 1973 ዓ.ም. ሦስት ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ በወሰነው መሠረት፣ ሐምሌ 12 ቀን 1973 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሦስተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ አንብሮተ እድ፣ አባ ገሪማ ተብለው የሱዳንና የኑብያ ኤጲስ ቆጶስ ኾነው እንዲሠሩ ተሹመዋል፡፡

ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ፣ የኤጲስ ቆጶስነቱን ሥራ እንደያዙ በ1975 ዓ.ም. የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሓላፊ ኾነው እንዲሠሩ ተመድበዋል፡፡ ብፁዕነታቸው፣ ወደ ልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በመጡበት ወቅት፣ የዝናም እጥረት ባስከተለው ድርቅ ምክንያት ከፍተኛ ችግር ተፈጥሮ ስለነበር፣ የአገር ውስጥና የውጭ ርዳታ ሰጭዎችን በዓለም አቀፍ መድረክ ተዘዋውረው በማስተባበር፣ በየአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤቶች አማካይነት የርዳታው ስርጭት ለኹሉም ሕዝበ ኢትዮጵያ ያለምንም ልዩነት እንዲዳረስ በማድረግ ግዴቸውን ተወጥተዋል፡፡

በመቀጠልም በ1982 ዓ.ም. የጋምቤላ እና የኢሉባቦር ጠቅላይ ግዛት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ሠርተዋል፡፡ በ1984 ዓ.ም.፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ኾነው ሠርተዋል፡፡ የጸሐፊነቱን ሥራ እንደ ያዙ በ1985 ዓ.ም. የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሓላፊ በመኾን አገልግለዋል፡፡

በዚኹ በ1985 ዓ.ም.፣ የምዕራብ ጎጃም እና የመተከል አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው እንዲሠሩ ተመድበዋል፡፡ በ1986 ዓ.ም. በመንግሥት ተወስዶ የነበረው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተመልሶ በአዲስ መልክ ሲዋቀር የኮሌጁ ዲን ኾነው ሠርተዋል፡፡ የኮሌጁ የሓላፊነት ድርሻ እንዳለ ኾኖ፣ በ1987 ዓ.ም. በሊቀ ጳጳስ ደረጃ የመጀመሪያው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኾነው ተመድበው ሠርተዋል፡፡

የብፁዕ ዶር. አቡነ ገሪማ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ፤ “ጽ/ቤታቸውን ዋልድባቸው ያደረጉ፣ ዓላማ ያላቸው ሥራ ወዳድ ነበሩ”/ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ/ (4)

ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ፣ ከ1990 ዓ.ም. ጀምሮ፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት እና የውጭ ግንኙነት መምሪያ የበላይ ሓላፊ ኾነው ሠርተዋል፡፡ እንዲሁም ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በያዙት ሥራ ላይ የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው አገልግለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ሥራ ብቻ ሳይወሰኑ በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የበላይ ተጠሪ ኾነው ሠርተዋል፡፡

ለማስረጃም ያህል

  • የገነተ ኢየሱስ ገነተ ማርያም
  • የአንቀጸ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል፣
  • የምስካየ ኅዙናን መድኀኔ ዓለም
  • የቦሌ ደብረ ሳሌም መድኀኔ ዓለም እና መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ካቴድራል ዋና ተጠሪ በመኾን አገልግለዋል፡፡

ከዚህ የሥራ ቆይታ በኋላ በ1997 ዓ.ም.፣ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ በመኾን አገልግለዋል፤ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላም በ1998 ዓ.ም. ወደ እናት አገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰው፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት እና የውጭ ግንኙነት መመሪያ የበላይ ሓላፊ ኾነው ይሠሩ ዘንድ ተመድበዋል፡፡

ብፁዕነታቸው፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊ ተልእኮ አፈጻጸም በተመደቡበት የሥራ ዘርፍ ኹሉ መልካም የሥራ ውጤት በማበርከት የሚታወቁ ሲኾን፣ በተለይም የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሕንፃ ሥራ ዐቢይ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ ኾነው ከመሥራት ጋራ በተለያዩ ኮሚቴዎች እና ቦርዶች ውስጥ ሰብሳቢ ኾነው አገልግለዋል፡፡

ብፁዕነታቸው፣ በዓለም አቀፍ ጉባኤያት ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ፣ የጉባኤ ልኡካን መሪና ተሳታፊ የኾኑባቸው ብዙዎች ናቸው፤ ጥቂቱን ለማዘከር ያህል፤

  • በዓለም አብያተ ክርስቲያናት እና በአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣
  • በኢጣሊያ- ራቢና፣
  • በዛምቢያ -ኬትዊ፣
  • በኬንያ-ናይሮቢ፣
  • በኦስትሪያ – ቬናና
  • በምዕራብ ጀርመን – ቦን ያደረጓቸው የሥራ ተልእኮዎች በታሪክ መዛግብት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት እና የውጭ ግንኙነት የበላይ ሓላፊነት ሥራቸውን እንደያዙ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ፕሬዚዳንት ቢሮ ዋና ጸሐፊ ኾነው አገልግለዋል፡፡

ብፁዕነታቸው፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያጋጠማቸው የጤና ዕጦት ችግር ቢፈታተናቸውም፣ ሕመማቸውን በሕክምና እየተከታተሉ ምድብ ሥራቸውን ከማከናወን የተገቱበት ጊዜ አልነበረም፡፡ ኾኖም ሕመማቸው ከአቅም በላይ እየኾነ መምጣቱን የተመለከቱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ወደ ሕክምና ማዕከል እንዲሔዱ ባዘዙት መሠረት፣ በደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ሲታከሙ ቆይተው፣ በኵረ ትንሣኤ ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጠፋውን ዓለም መልሶ ለሰው ልጆች የቸርነቱን ሥራ ሠርቶ በተነሣ ማግሥት፣ ሚያዝያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ማጠቃለያ

ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ፣ ሰፊ በኾነው አገልግሎታቸው፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን የሚጠቅሙ፣ የአእምሮአቸው ጭማቂ የኾኑ ሥነ ጽሑፎችንና ጥናታዊ ጽሑፎችን ለየተመደበው ሥራና አገልግሎት በየወቅቱ ሲያበረክቱ ኑረዋል፡፡

በልዩ ልዩ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸው፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዓበይት በዓላትና ለየክብረ በዓሉ የሚገባውን ክብርና መግለጫ በማዘጋጀት፣ የትምህርተ ሃይማኖት፣ የታሪክ እና የሥርዓተ እምነት ትውፊቶችን ጭምር የሚገልጹ ጽሑፎችን ከነማስረጃዎቻቸው በማቅረብ ለጥናት እና ምርምር አድራጊ ሊቃውንት የጎላ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ ዕውቀት ለሚገኝበት ነገር ኹሉ ጊዜያቸውን ሳይቆጥቡ ሲጽፉ፣ የተጻፈውን ሲያርሙና ሲያመሠጥሩ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋራ ሲያመሳክሩ፣ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ቋሚ ምስክርና ኣርአያ በመኾን የሠሩ አባት ነበሩ፡፡

ብፁዕነታቸው የሥነ ጽሑፍ ሰው እንደ መኾናቸው መጠን፣ ለኅትመት የሚበቁ በርከት ያሉ ዝግጅቶች ቢኖሯቸውም፣ አሁን በሥራ ለኅትመት በቅተው ለአንባብያን ከተላለፉት መካከል፡-

  1. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በየዘመናቱ
  2. ትምህርተ ሃይማኖትሚል ስያሜ ያሳተሟቸው ኹለት መጻሕፍት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የብፁዕ ዶር. አቡነ ገሪማ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ፤ “ጽ/ቤታቸውን ዋልድባቸው ያደረጉ፣ ዓላማ ያላቸው ሥራ ወዳድ ነበሩ”/ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ/ (5)

ብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ፣ በሥራ ዓለም ቆይታቸው የሥራን ክቡርነት የተረዱ፣ የአገራችንና የቤተ ክርስቲያናችን ፍቅር የሚያገብራቸው፣ የየዕለቱን የተግባር እንቅስቃሴ ለመሸፈን ድካም የማይበግራቸው ቅን፣ ታዛዥና መላ ሕይወታቸውን በሥራ ያሳለፉ ታላቅ አባት ነበሩ፡፡ ዳሩ ግን፣ መኑ ሰብእ ዘየሐዩ ወኢይሬእያ ለሞት በተባለው አምላካዊ ቃል መሠረት፣ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው፣ ሚያዝያ 27 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ በተወለዱ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

አስከሬናቸውም፣ ሚያዝያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተወስዶ ጸሎተ ፍትሐት ሲደረግበት፣ ሲጸለይበትና ሲቀደስበት ካደረ በኋላ፤

  1. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በተገኙበት፤
  2. ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ወኤጲስ ቆጶሳት፤
  3. የጠቅላይ ቤተ ክህነት እና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች፤
  4. የአዲስ አበባ ገዳማት እና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣
  5. ዘመድ ወዳጅ ቤተ ሰዎቻቸው ባሉበት የቀብራቸው ሥነ ሥርዓት፣ ሚያዝያ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ነፍሳቸውን ለወዳጆቹ ጻድቃን ወሰማዕታት በአዘጋጀው መካነ ዕረፍት ያሳርፍልን፡፡

በብፁዕ ዶክተር አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኛችኹትን ኹሉ በቤተ ክርስቲያናችን ስም እናመሰግናለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

ለብፁዕ አባታችን ጽ/ቤታቸው ዋልድባቸው ናት
/ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፤ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ/

“… ብፁዕ አባታችን በተማሪ ቤት፣ የወጣትነት ጠባይዕ ያላሸነፋቸው፣ አንጋፋ የቤተ ክርስቲያን ልጅ እንደነበሩ፡፡ ምንኵስናውንም፣ ቁምስናውንም፣ ቅስናውንም ጵጵስናውንም ያገኙት በጽኑ ሃይማኖታቸው ነው፡፡ ቅድስናን፣ ድንግልናን፣ አገልግሎትን አስተባብረው ይዘው በመገኘታቸው ኹሉ ነገር የተፈጸመላቸው፡፡ ያቺ ጠባብ ዋሻ ለእያንዳንዱ መነኵሴ ካወቅባት ዋልድባ ናት፡፡ ለብፁዕ አባታችን ይህቺ እዚህ የነበረች ጽ/ቤታቸው ዋልድባቸው ናት፤ ዓላማቸውን አላስታጎለችባቸውም፤ ጠንክረው በዓላማቸው ጸንተው አገልግሎት በመስጠታቸው ኹሉም ሥፍራ ደርሰውበታል መንፈሳዊውን ማዕድ፤ ተከናውኖላቸዋል፡፡

ብፁዕ አባታችን የጽሑፍና የታሪክ ምሁር፣ ሊቅ በመኾናቸው፣ “በቃል ያለ ይወረሳል፤ በመጽሐፍ ያለ ይወረሳል” የሚለውን ከማንም በላይ ያምኑበታል፡፡ ማንኛውንም ነገር ብዕር ሳያስጨብጡ፣ በጽሑፍ ሳያሰፍሩ አያቀርቡትም፡፡ አጣርተው፣ አርመው፣ አስተካክለው ያቀርቡታል፡፡ በሥራቸው ኹሉ ምቹ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ አባት ናቸው፡፡

ብፁዕ አባታችን በጠረፍ ጠባቂነት እንደተመደበ ግዳጅ ጠባቂ ወታደር ነበሩ፡፡ በጠረፍ ላይ ድንበር ጠባቂ ኾኖ የተመደበ ግዳጅ ፈጻሚ ወታደር፣ መሣሪያውን ወድሮ የበላይ አዛዡ ምታ ተኩስ ሲለው ፋታ ሳይሰጥ ይተኩሳል፤ ያለትእዛዝ ግን አይሠራም፡፡ ብፁዕነታቸው እንደዚሁ ብዕራቸው እንደ መሣሪያ ነው፤ የበላያቸውን ትእዛዝ ይጠብቃሉ፤ ይህ ይጻፍ፣ እንዲህ ይባል ከተባሉ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ አንዳንዶቻችን ደግሞ ጠንከር ያለ ኾኖ ስናገኘውና ለምን እንደዚህ ተጻፈ ስንላቸው፣ “ቤተ ክርስቲያን አዛለች” ብለው ነው የሚመልሱት፡፡ ትእዛዝ ፈጻሚ ነበሩ፡፡

እኔ አኹን ራሴን እንኳ እጠራጠራለኹ፤ በአኹኑ ዘመን፤ አስቸጋሪ ጊዜ ነው፤ ዓላማውን ጠብቆ ሃይማኖቱ ሳይዛባ፣ ምንኵስናውን ንጽሕናውን እንደጠበቀ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገለ እዚህ የደረሰ አባት ያስቀናል፡፡ መጨረሻው ካልደረሰ ሰው ያጠራጥራል፤ አኹን ፍጻሜአቸው አምሮላቸዋል፤ ቅድስናቸውን፣ ሃይማኖታቸውን፣ ዓላማቸውን እንደጠበቁ መጠራታቸው – በ94 ዓመታቸው፡፡ እኔ እንደውም ስገምት በዕድሜ ከእኛ በታች ይመስሉኝ ነበር፡፡ ከተሰጠው በላይ ነው የተሰጣቸው፡፡ 70 እና 80 ዘመን ነው በእግዚአብሔር የታዘዘው፡፡ 120 በኖኅ ዘመን ነው የተወሰነው፡፡ ከዚያ ደግሞ እየወረደ መጥቶ፣ 70 እና 80 ኾኗል፡፡ አኹንም አልሠራኽም ብሎ የሚቀወቅሰኝ አለ ብለው ይፈራሉ፤ ለምንድን ነው የማያርፉት ያልኋቸው ጊዜ አለ፡፡ “ጨርሶ እወድቃለኹ፤ እዚያው ይሻለኛል” ብለውኛል፡፡ ሥራ ወዳድ፣ ዓላማ ያላቸው ናቸው፡፡

የተወለዱበት ቦታም ቅድም ተጠቅሷል፡፡ አንድ እዚህ የደረሰ ዘመድ የለም፡፡ ተሳስቶ ወይም ናፍቆ አንዱ ብቅ ቢል፣ “ዓላማህም አይደል፤ ምን አመጣኽ?” ብለው ያሰናብቱታል፡፡ የወር ደመወዛቸውን ባንክ አያውቅም፡፡ በጣም ቆራጥ እውነተኛ መናኝ ናቸው፡፡ ታላቅ አባት አጥተናል፤ ነፍሳቸው ግን ታርፋለች፤ “አዕርፍ ነፍሰ አቡነ ገሪማ” እያለን እንጸልያለን፤ እግዚአብሔር በረድኤት አይለየን፡፡”

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

ከብፁዕ አቡነ ገሪማ የምንማረው ታማኝነት፣ ታዛዥነት፣ ጥብዓት ነው፤ ቤተ ክርስቲያናችን ጠንካራ ኾና ብዙ ደረጃ ላይ ትደርስ ነበር
/ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/

ብፁዕነታቸው በታሪካቸው እንደተነገረው ኹሉ፣ በቤተ ክርስቲያን ያላቸው ጥብቅ የኾነ መንፈሳዊ አባትነት፣ የሚደነቅ እንደኾነ በታሪካቸው ተጠቅሷል፤ በትምህርቱም ተነሥቷል፡፡ በተመደቡበት ሥራ ኹሉ ወደፊት ወደኋላ፣ ወደ ቀኝ ወደ ግራ ሳይሉ ሥራቸውን አጥብቀው የሚሠሩ፣ ሥራቸውን እንደ ሃይማኖት አጥብቀው የያዙ ነበሩ፡፡ በታማኝነት፣ በሐቀኝነት፣ በእውነተኛነት ሥራቸውን አክብረው በሕመም ተይዘው እስካቃታቸው ድረስ በመሥሪያ ቤታቸው አይቀሩም ነበር፡፡

እንደ ብፁዕ አቡነ ገሪማ በታማኝነት፣ በጥንቃቄና በጥብዓት ብንሠራ ኖሮ ቤተ ክርስቲያናችን ጠንካራ ኾና ብዙ ደረጃ ላይ ትደርስ ነበር፡፡ ኹላችንም እንደ እርሳቸው በቆራጥነት፣ በተጠያቂነት፣ በሓላፊነት ጠንክረን ብንሠራ፣ ቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ትኾናለች፡፡ ከብፁዕ አቡነ ገሪማ የምንማረው ይህን ነው በእውነቱ – ታማኝነት፣ ታዛዥነት፣ ጥብዓት፡፡ ማናቸውንም ዕውቀትና ጉልበት ኹሉ ለቤተ ክርስቲያን ያበረከቱ ትልቅ አባት ነበሩ፡፡

እንግዲህ ቅዱስ ጳውሎስ፣ መልካሙን ገድል ተጋድያለኹ፤ ሩጫዬን ጨርሻለኹ፤ ሃይማኖቴን ጠብቄአለኹ፤ በዕለተ ምጽኣት ለቅዱሳኑ፣ ለአገልጋዮቹ፣ ለታማኞቹ የሚያድለው የጽድቅ አክሊል ለብፁዕ አቡነ ገሪማ እንደተዘጋጀላቸው፣ የኹላችንም እምነት ነው፡፡ ኹሉም ሥራ ቢሠራ፣ የበኩሉን ድርሻ ቢያበረክት ጥሩ ነው፡፡ ጽናት፣ ታማኝነት፣ ጥብዓት፣ ጥንካሬ ግን ይጎድለናል፡፡ ብፁዕ አቡነ ገሪማ ይኼ አልነበረባቸውም፡፡ ሥራቸውን ፈጽመው ወደ አምላካቸው ተጉዘዋል፡፡ በመንግሥቱ እንደሚቀበላቸው የኹላችንም እምነት ነው፡፡

በዚህ ሽኝት የተገኛችኹትን፣ በዚህ በዐውደ ምሕረት የተሰበሰባችኹትን ኹሉ እግዚአብሔር ይባርክልን፤ እግዚአብሔር ይጠብቃችኹ፤ ብፁዕነታቸውንም በመንግሥቱ ይቀበልልን፡፡ አሜን፡፡

Top Articles
Latest Posts
Article information

Author: Dong Thiel

Last Updated: 04/05/2023

Views: 5303

Rating: 4.9 / 5 (79 voted)

Reviews: 86% of readers found this page helpful

Author information

Name: Dong Thiel

Birthday: 2001-07-14

Address: 2865 Kasha Unions, West Corrinne, AK 05708-1071

Phone: +3512198379449

Job: Design Planner

Hobby: Graffiti, Foreign language learning, Gambling, Metalworking, Rowing, Sculling, Sewing

Introduction: My name is Dong Thiel, I am a brainy, happy, tasty, lively, splendid, talented, cooperative person who loves writing and wants to share my knowledge and understanding with you.