ጉዞ ዓድዋ - የጀግኖችን ዳና የተከተሉ ተጓዦች ታሪክ - BBC News አማርኛ (2023)

ጉዞ ዓድዋ - የጀግኖችን ዳና የተከተሉ ተጓዦች ታሪክ - BBC News አማርኛ (1)

የጽሁፉ መረጃ
  • ፀሐፊ, በያሬድ ሹመቴ
  • የሥራ ድርሻ, የጉዞ ዓድዋ አስተባባሪ

እንዳ አባ ገሪማ

የእንዳ አባ ገሪማ ካሕናት የበዓል ልብሰ ተክህኗቸውን ለብሰው፤ ቀሳውስቱ የሚያብረቀርቅ መጎናጸፊያ አጊጠው የዕጣን ማጠኛ ጽንሃቸውን ይዘው፤ ዲያቆናት በመጾር መስቀል በወርቅ ዣንጥላ ተንቆጥቁጠው፤ መሪጌቶች ግራ እና ቀኝ የቤተ ክርስቲያኑ ዐውደ ምህረት መወጣጫ ላይ እዚህም እዚያም እጅብ ብለው ተቀምጠዋል።

በጥንግ ድርብ ልብሳቸው ተውበው እጄታቸው ከብር የተሠሩ መቋሚያቸውን ተደግፈው ለዐውደ ዓመት የሚወጣ ጽናጽላቸውን እንደያዙ ይጠባበቃሉ።

መሬት ላይ ግዙፍ ከበሮዎች ተደግፈው የተቀመጡ ልጅ እግር ሊቃውንት እንግዶቻቸውን ጥበቃ በር በር ያያሉ።

የአንድ ቀበሌ ሙሉ ሚሊሻዎች የጠመንጃቸውን ሰደፍ በመዳፋቸው ጨብጠው አፈሙዙን ትከሻቸው ላይ እንዳስደገፉ ግራ እና ቀኝ ተሰልፈው "ቱታ" እያሉ በፉከራ ወደ ቤተክርስቲያኑ ግቢ ዘለቁ።

የትምህርት ቤታቸው መለያ ልብሳቸውን የለበሱ ተማሪዎች፤ የሚበላ ምግብና የሚጠጣ ጠላ የተሸከሙ እናቶችን ከፊት አስቀድመው እንግዶቹን አጅበው ብቅ አሉ።

የአባ ገሪማ ገዳም ሊቃውንት እንግዶቹ መድረሳቸውን አይተው ከየተቀመጡበት ተነስተው ዐውደ ምህረቱ ላይ ተሰየሙ።

እልልታው ዝማሬውና ጭብጨባው ደመቀ።

የጉዞ ዓድዋ 1 የመጀመሪያ አምስት ተጓዦች ከአዲስ አበባ በእግራቸው 43 ቀናት ተጉዘው የዓድዋ ተራሮች ታሪካዊ መካነ እምብርቱ ላይ እንዳ አባ ገሪማ ገዳም የካቲት 21 ቀን 2006 ዓ.ም እኩለ ቀን ላይ ደረሱ።

የዶጋሊ እና የዓድዋው ጀግና ራስ አሉላ እንግዳ (አባ ነጋ) የእረፍት መካን፤ የዓለማችን ቁጥር አንድ ጥንታዊው መጽሐፍ ቅዱስ መገኛ፤ ግርማ ሞገስ ከተላበሱ የሰማይ ምሶሶ መሳይ ተራሮች መሐል የሚገኘው የእንዳ አባ ገሪማ ገዳም የንግሥ በዓል እንጂ እግረኛ ተጓዦችን ለመቀበል የወጣ አጀብ የማይመስል ትልቅ ትዕይንት አስተናገደ።

ሊቃውንቱ በቅኔ ስለ ዓድዋ ተቀኙ፤ መዘምራኑም ለዚያች ቀን በሰላም ያደረሰን አምላክ ይመስገን ሲሉ “ንሴብሖ” በማለት በወረብ ጀምረው በቸብቸቦ አሳረጉት።

ሁሉም ነገር ውብ ነበር። በፍጹም የማይረሳ!

የመጀመሪያው ጉዞ ዓድዋ።

ስንብት በአላማጣ

ከሰባት ዓመታት በኋላ በ8ኛው ጉዞ ዓድዋ 97 ተጓዦች ከአዲስ አበባ ተነስተው ለ26 ቀናት 600 ኪሎ ሜትሮችን በእግራቸው ከተጓዙ በኋላ ለ10 ቀናት አላማጣ በሚገኝ አንድ ሕንጻ ውስጥ እንደ እስረኛ ታጉረው ተቀምጠዋል።

ከዛሬ ነገ “እንሄዳለን” በማለት በጉጉት የሚጠብቁት ተጓዦች፤ ዓድዋ ሳይደርሱ ጊዜው ሊጠናቀቅ መኾኑን በማሰብ በከፍተኛ መረበሽ ስሜት ውስጥ ሆነው አመላቸው ለራሳቸው ጭምር እስኪያታክታቸው ተሰላችተዋል።

የካቲት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. የጉዞው መጠናቀቂያ ቀን ነበር።

ከአላማጣ 400 የኪሎሜትር ያህል ጉዞ ይቀራል፣ የቀረው ቀን ግን የአንድ ሳምንት ጊዜ ያህል ብቻ ነው።

በአማካኝ በአንድ ቀን ውስጥ 30 ኪሎ ሜትሮችን የመጓዝ አቅም ያላቸው ተጓዦች በቀራቸው ጊዜ ዓድዋ መድረስ እንደማይቻል ቢገባቸውም፤ በቀን እስከ 50 ኪሎ ሜትሮች በመጓዝ እንደርሳለን የሚል እልህ ውስጥ ቢገቡም በአንድ ቦታ “ታስረው” መቀመጣቸው ተስፋቸውን እያመነመነው መጥቷል።

ሕንጻው የመከላከያ ሠራዊት ጊዜያዊ ካምፕ ነው። የሲቪል አገልግሎት መስጫ የነበረው ባለ አራት ፎቅ ሕንጻ እና ቅጥር ግቢው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ወደ ጦር ካምፕነት ተቀይሯል።

ወታደሮቹ ከተጓዦች ጋር በእጅጉ ተላምደዋል። ምግብ በጋራ ሲበስል ሽንኩርት በመላጥ ጭምር እያገዙ ሰንብተዋል።

በዚህ ቆይታ መሐል መርዶው መጣ።

ሰፊ አዳራሽ ውስጥ ከመቶ ያላነሱ ተጓዦች እና አስተባባሪዎች ለምክክር ተቀምጡ።

ከጉዞ አስተባባሪዎች መሐል አንደኛው ከአካባቢው የመከላከያ አመራሮች ጋር የተደረገውን ውይይት አጠር አድርጎ በማቅረብ ከዚህ በኋላ ያለውን ጉዞ ማድረግ በፍጹም የሚቻል አለመኾኑን አረዳቸው።

ድንጋጤ እና መረበሽ አዳራሹን ወረረው።

“ኮሌኔሉ እንደነገረን ከኾነ...” አለና መናገር ቀጠለ “ከዚህ በኋላ ያሉ መንገዶች በሙሉ የተቆራረጠ ውጊያ አለ። መሬቱ ፈንጅ ይኑረው አይኑረው አይታወቅም። እናንተን ዓድዋ ይዘን መድረስ የምንችለው በግራ እና በቀኝ አጅበን ሲሆን ብቻ ነው።

“ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የወታደራዊ ቀጠና ትኩረት ስለምትስቡ ለጥቃት ያጋልጣችኋል...ከረዥም ርቀት በመድፍ ልትመቱ ወይንም በድንገት የሽምቅ ጥቃት ሊደርስባችሁ ይችላል።

“እኛም በሚፈጠሩ ጥርጣሬዎች ሁሉ ድንገተኛ እርምጃ ብንወስድ ሰላማዊ ሰው ሊጎዳብን ይችላል... መሔዳችሁም መቅረታችሁም ኪሳራ ነው... ከሁለቱ ኪሳራ ደግሞ የሚመረጠው መቅረታችሁ ነው። ምክንያቱም በመቅረታችሁ ከሞት ትተርፋላችሁ።”

የጉዞውን መቋረጥ የሰማ ተጓዥ አዳራሹን ወደ ለቅሶ ቤት ለወጠው።

“እኔ የማለቅሰው ዓድዋ ባለመድረሴ አይደለም” አለች አንዲት የሁለት ልጆች እናት የሆነች ተጓዥ ዕንባዋን እየዘረገፈች።

“እኔ የማለቅሰው ዓድዋ ባለመድረሴ አይደለም፤ ዓድዋ መድረስ ያልቻልኩበት ምክንያት ነው የሚያስለቅሰኝ። አገሬ እንዲህ ሆና እርስ በእርሳችን ተቋስለን መተያየት የማንችልበት ዘመን ላይ በመድረሳችን ለልጆቼ የማስረክባት አገር ተስፋ አልባነት ነው የሚያስለቅሰኝ።”

“ይከበር፣ ይዘከር ለዘላለም”

ጉዞ ዓድዋ የተመሰረተው በ2006 ዓ.ም. ከዛሬ ዘጠኝ ዓመታት በፊት ነበር።

ከተጓዦች መሐል የፊልም ባለሙያ የኾነው ሙሉጌታ መገርሳ አማሩ ለጉዞው ጥንስስ መነሻ ሀሳብ አፍላቂው እሱ ነበር።

ሙሉጌታ መገርሳ በፊልም ሙያ ውስጥ አዳጋች የሆኑ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን እና የአካል አደጋ ሊከስቱ የሚችሉ ትዕይንቶችን ዋናዎቹን ተዋንያን ተክቶ በመሥራት ተዋቂነትን ያተረፈ (ስታንት) ሙያተኛ ነው።

የራዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ እና የፊልም ሙያተኛ የሆነው ጋዜጠኛ ብርሐኔ ንጉሤ ጋር በአንድ ወቅት ሙሉጌታ መገርሳ እና የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በጋራ በመኾን አጭር ፊልም ይሠሩ ነበር።

ወደ ዓድዋ የእግር ጉዞ የማድረግ ፍላጎታቸውንም አስረድተውት በምን ሊተባበራቸው እንደሚችል ይጠይቁታል።

ብርሐኔ ንጉሤ በሀሳቡ በመደሰቱ በዓድዋ ድል ላይ የሚሠሩ አንዲት ባለሐብት እንደሚያውቅ እና እሳቸውን ብናገኛቸው የጉዞውን ወጪ የሚሸፍን ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተስፋ በማድረግ የሚችለውን እንደሚሞክር ገለጸ።

ጋዜጠኛ ብርሐኔ የተባሉትን ባለሐብት ለማግኘት እንደ መሰላል መጠቀም የፈለጋቸው ሰው ደግሞ እውቁ ፖለቲከኛ አቶ ስብሐት ነጋ (አቦይ ስብሐት) ነበሩ።

አቦይ ስብሐትን በስልክ እንዳናገራቸው እና ድጋፍ ያደርጋሉ የተባሉት ባለሐብት በአገር ውስጥ ባለመኖራቸው ነገር ግን እሳቸው ሀሳቡን የመስማት ፍላጎት ስላደረባቸው በማግስቱ ወደ ቢሯቸው በመሄድ ምክክር እንዲያደርጉ ጋበዟቸው።

አቦይ ስብሐት በሰዓቱ በቢሯቸው ተገኝተዋል። ጋዜጠኛ ብርሐኔ ይዟቸው የገባውን የቀረጻ ባልደረቦቹን አስተዋውቆ የጉዞውን ዓላማ አጠር አድርጎ አስረዳቸው።

አቦይ ስብሐት የጋዜጠኛ ብርሃኔን ገለጻ አይናቸውን ጨፍነው ሲያደምጡ ከቆዩ በኋላ ንግግሩን ሲጨርስ ለሌሎቹ ሁለት ሰዎች በጣታቸው እየጠቆሙ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠየቁ።

ሰውዬውን ከዚህ ቀደም አይቷቸው ለማያውቅ ሰው በደጅ ከሚነገረው ዝናቸው አንጻር ፍርሐት የሚያሳድር ምስል ያላቸው ቢኾኑም እንኳን በጽህፈት ቤታቸው ለተቀበሏቸው እንግዶች ፍርሐታቸውን የሚያስለቅቅ አቀራረብ ነበራቸው።

ሁለቱም በየተራ የጉዞውን ዓላማ በአጭሩ አስረዱ።

አቦይ ስብሐት ሁሉም ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ለአፍታ ቆይታ ዐይናቸውን እንደጨፈኑ ጸጥ አሉ።

ረጋ ባለ ድምጽ የተመጠኑ ቃላት ብቻ እያወጡ መናገር ጀመሩ።

ለዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ንግግራቸውን ቃል በቃል ወረቀት ላይ መዝግቦ ለማስቀረት የማያግድ ረጋ ያለ አቀራረብ ስለነበራቸው ጸሃፊው አንዱንም ቃላቸውን ሳያስቀር መመዝገብ ችሎ ነበር።

የእግር ጉዞ ማድረግ እምብዛም ከባድ አለመኾኑን ሳቅ በሚያጭር ንግግር አዋዝተው ከገለጹ በኋላ፣ ሐሳቡ ግን ግዙፍ መኾኑን ተናገሩ።

“እኛ ከደደቢት ተነስተን አዲስ አበባ የደረስነው እየተዋጋን ስለነበር 17 ዓመት ፈጅቶብናል። እናንተ ግን ውጊያ ስለሌለባችሁ እንኳን እንደኛ 17 ዓመት ይቅርና እንደ አፄ ምኒልክ ሠራዊት አምስት ወር አይፈጅባችሁም” ሳቅ ካሉ በኋላ ትንሽ አፍታ ወስደው መናገር ቀጠሉ።

“እንደ አፄ ምኒልክ ሠራዊት አምስት ወር አይፈጅባችሁም ያልኩት ደግሞ በየአገሩ አቀባበል እና ድግስ ስለማይበዛባችሁ ነው” ብለው ረዘም ያለ ሳቅ ሳቁ፤ ሁሉም በፈገግታ አጀቧቸው።

የተመጠኑ ቃላቶችን ተጠቅመው ሐሳባቸውን በሚገባ ካቀረቡ በኋላ፣ ጉዞ ምን ቢመስል ጥሩ እንደሚኾን ሐሳብ ሰነዘሩ።

ተጓዦች በዛ ማለት ቢችሉ እና የየጦር አዛዦችን እየወከሉ ቢጓዙ መልካም መኾኑን ተናገሩ። የጉዞው ፍጻሜ ቀንም ምን አይነት አቀባበል ሊኖር እንደሚገባ ጭምር ሐሳብ ሰጡ።

በመሐል ደግሞ የጉዞው ሐሳብ ቢኾን መልካም ነው ብለው ያሰቡትን መሪ መፈክር አቀረቡ።

“ይከበር ይዘከር ለዘላለም” ይህ ሐሳብ የዚያን ጊዜ ተመዘገበ። ጉዞ ዓድዋ በቆየባቸው ዓመታት ሁሉ የጉዞው መፈክር በመኾን አገልግሏል።

ስለ ጉዞው ወጪ ድጋፍ ጉዳይ “ሐሳባችሁን በጽሑፍ አቅርቡልኝና ለባለሀብቷ ሲመለሱ እሰጥላችኋለሁ” በማለት ንግግራቸው ጨርሰው እንግዶቻቸውን አሰናበቱ።

ጉዞ ዓድዋ በታቀደው የጉዞ መርሐ ግብር መሰረት የመጀመሪያው ቀን እየተቃረበ መጣ። በአቶ ስብሐት በኩል ይገኛሉ የተባሉት ባለሀብት ግን ወደ አገር አልተመለሱም።

የዚህን ጊዜ ጋዜጠኛ ብርሐኔ ንጉሤ ጉዞውን ራሱም ለመጓዝ መወሰኑን በመግለጽ ኪሳችን ውስጥ ባለን ገንዘብ ጉዞውን እንጀምረው በማለት ጓዶቹን አደፋፈረ።

ጉዞውን ለመጀመር የሚያስችል በጀት ባይኖርም እንኳን አዲስ አበባን ለቆ ለመውጣት መንግሥት ፍቃድ የሰጠበትን ደብዳቤ መያዝ አስፈላጊ በመኾኑ የጉዞውን ዓላማ የሚያስረዳ ደብዳቤ በመጻፍ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር የፍቃድ ደብዳቤ እንዲሰጥ ጠየቅን።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምንም አይነት ምላሽ ሳይሰጥ ዝምታን መርጦ ቆየ። የቀኑን ማጠር ግምት ውስጥ በመክተት አማራጭ ሐሳብ ተፈለገ፤ በወቅቱ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሬድዋን ሁሴን በዚህ ጉዳይ ላይ የትብብር ደብዳቤ እንዲጽፉ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ደውሎ ጠየቃቸው።

አቶ ሬድዋን ሁሴን ሀሳቡን እንደወደዱት እና በአስቸኳይ በማግስቱ ደብዳቤውን ከጽህፈት ቤታቸው መጥቶ መውሰድ እንደሚቻል ገልጸው ደብዳቤው ተጻፈ።

ለጉዞው ድጋፍ ያደርጋሉ የተባሉት ሰው በአገር ውስጥ ስላልተገኙ፣ አቦይ ስብሐት “በተስፋ ስላስጠበቅኳችሁ በመጠኑ እንዲረዳችሁ ከግሌ ይህንን ብር እንኩ” በማለት የጉዞ ዓድዋ የመጀመሪያ መዋጮ 15,000 ብር በካኪ ጠቅልለው ሰጧቸው።

ለሎጂስቲክስ ማመላለሻ የሚኾን ከአዲካ ባለቤት ከአቶ አዋድ መሐመድ በውሰት በተገኘ ፒክ አፕ መኪና እና ከአቶ ስብሐት ነጋ በተበረከተ 15,000 ብር ጉዞው ሊጀመር ቀን ተቆረጠ።

ጉዞ ዓድዋ ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ ተጓዦች ደብረ ብርሐን እስኪደርሱ ድረስ በየትኛውም ሚዲያ ይህ ጉዞ ሳይዘገብ በምስጢር ተይዞ ቆየ።

የአፄ ምኒልክ ትርክት እና ጉዞ ዓድዋ

ጉዞ ዓድዋ ባሳለፋቸው ስምንት የጉዞ ዓመታት ሁሉ የአፄ ምኒልክ ጉዳይ አነታራኪነቱ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ ባለመምጣቱ በጉዞው ላይ ራሱን የቻለ በርካታ ገጠመኞችን አስተናግዷል።

አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዳር እስከዳር በአንድነት አሰልፈው ጦሩን በብቃት መርተው ለውጤት ያበቁ በዓለም የነጻነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና የነበራቸው ሰው መኾናቸው እንኳንስ ታሪክ እያጠና ለሚጓዝ የጉዞ ዓድዋ አባል ይቅርና ለማንኛውም ሰው ግልጽ የሆነ እውነታ ነው።

የመጀመሪያው የጉዞ ፈተና ተብሎ ሊወሰድ የሚችለው በአፄ ምኒልክ ዙሪያ በጉዞው ጅማሬ ወቅት ሚዲያውን ተቆጣጥሮት የነበረው ትርክት ነው ብሎ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ያምናል።

በተለይም ከአኖሌ ሐውልት መመረቅ ጋር በተያያዘ በወቅቱ በቴሌቪዥን ቀርቦ የነበረው ዘገባ እና እሱን ተከትሎ በርካታ የወቅቱ ጋዜጦች እና መጽሔቶች፣ ከዚያም አልፎ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ለዘገባው የሰጧቸው ምላሾች የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ስም አንስቶ ጉዞ ለሚያደርግ ሰው የደኅንነቱ ጉዳይ አሳሳቢ ነበር።

በዚህም ምክንያት ጉዞው ደብረ ብርሃንን ከማለፉ በፊት በየትኛውም ሚዲያ ሳይዘገብ በምስጢር ተይዞ ቆየ።

በጉዞ ዓድዋ 1 ፍጻሜ ወቅት የካቲት 23 ቀን 2006 ዓ.ም. በዓድዋ ከተማ በሚገኘውና “ሰልፍ ሜዳ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ የከተማው ሕዝብ ነቅሎ ወጥቶ ተጓዦችን በክብር በተቀበለበት ሥነ ሥርዓት ላይ ጋዜጠኛ ብርሐኔ ንጉሤ በመድረኩ ላይ ያቀረበው ንግግር የመጀመሪያ አረፍተ ነገር የዳግማዊ አፄ ምኒልክን እና የእቴጌ ጣይቱን ስም አክብሮ በመጥራት የሚጀምር ነበር።

በሚቀጥሉት ተከታታይ ሦስት ዓመታት በተመሳሳይ መልኩ ዓድዋ ከተማ በሚገኘው ሰልፍ ሜዳ ላይ የዓድዋ ድል በዓል ቀን በደማቅ ማክበር ተለመደ።

በዚህችም ወቅት ሕዝቡ ግልብጥ ብሎ በመውጣት አዳራቸውን የሶሎዳ ተራራ አናት ላይ አሳልፈው የሚወርዱትን ተጓዦች በክብር ተቀብሎ አደባባዩ ላይ በተዘጋጀው መድረክ በጉዞው መሪ ንግግር ይደረጋል።

በዓድዋ እና አካባቢው ያሉ ታዳጊ ተማሪዎች ተጓዦችን ለመቀበል ሰልፍ ሜዳ የሚገኘውን ሕዝብ ትተው ወደ ተራራው አናት ቧጠው በመውጣት ለተጓዦች አቀባበል ማድረግም ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ልማድ ሆነ ቆዬ።

የዚህ ጊዜ አንድ ችግር ተፈጠረ። የሶሎዳ ተራራን ሽቅብ ወጥተው ተጓዦችን የሚቀበሉ ታዳጊ ተማሪዎች ያለ መሪ እና ደጋፊ በቁጥቋጦ የተሸፈነውን እና በሚናዱ አለቶች የተሞላው ግዙፍ ተራራ የታዳጊ ተማሪዎቹን እሽቅድድም ማስተናገድ ወደማይችልበት ደረጃ ደረሰ።

አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ በተከሰተ የአለት ናዳ ምክንያትም ዕድሜያቸው 11 እና 12 የሆነ ሁለት ታዳጊዎች ሕይወት አለፈ።

በዓሉ በሰልፍ ሜዳ ላይ ተከብሮ እንደተጠናቀቀ የታዳጊዎቹ ሞት ተሰማ። ተጓዦች የጉዞ ፍጻሜ ስኬታቸውን በፌሽታ የሚያሳልፉበት ቀን በቅጽበት በሐዘን ተዋጠ።

ሁሉም ተጓዥ ወደ ሟች ሕጻናቱ ቤተሰቦች እና ቤተክርስቲያን በነበረው የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ ለመታደም ሄዶ ሁሉም ሲላቀስ ውሎ አመሸ።

ይህ አጋጣሚ በታሪካዊው የዓድዋ ድል ዕለት ከነበረው ስሜት ጋር ተመሳስሎሽ ነበረው። ኢትዮጵያውያን የጣልያንን ጦር ሙሉ ለሙሉ ደምስሰው ድል በእጃቸው ማስገባታቸው ፌሽታ ሲፈጥር፤ ከኢትዮጵያ ወገን የወደቁ እልፍ ጀግኖች ሰማዕታት ደግሞ በጎን ይለቀስላቸው ነበር።

ከጉዞ ዓድዋ አንድ አንስቶ በተከታታይ ለአራት ዓመታት ያህል ግን በኦሮሚያ ክልል ከ80 ኪ.ሜትር ያልበለጠው የጉዞ መስመር እስኪታለፍ ድረስ በይፋ ከአዲስ አበባ ሽኝት ተደርጎ አያውቅም።

ነገሩ የተቀየረው በኅዳር ወር 2010 ዓ.ም የጣና ሐይቅ በእንቦጭ አረም መወረሩን ተከትሎ በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ እና በወቅቱ የነበሩ የኦህዴድ ባለሥልጣናት ወደ ባሕር ዳር ከክልሉ የተሰባሰቡ ወጣቶች እና የአገር ሽማግሌዎችን አስቀድመው “ጣና ኬኛ” በሚል መፈክር ባሕር ዳር ከተማ ባቀኑበት ጊዜ ነበር።

በዚህ ዓመት ተዘጋጅቶ በነበረው 5ኛው ዙር ጉዞ ዓድዋ ተሳታፊ የነበሩ 25 ተጓዦች ጥር 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ሆቴል ውስጥ በተዘጋጀ የመጀመሪያው የጉዞ ዓድዋ የሽኝት መርሐ ግብር በጥሩ መልኩ ተከናወነ። ተደብቆ የአምስት እና የስድስት ቀናትን መንገድ መጓዝ ቀረ።

ከዚያም አልፎ ከአዲስ አበባ መውጫ በር ጀምሮ ያሉ ሁሉም የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ለተጓዦች በሬ ጥለው ጭምር አቀባበል ማድረግ ጀመሩ። የነበረው ስጋት በሙሉ ተነነ።

በየመንገዱ ላይ ያጋጥሙ የነበሩ የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮች ተጓዦችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ሽሚያ ጀመሩ። “ድግስ ሲበዛ መንገድ ይረዝማል” የሚለው የአቶ ስብሐት ንግግር እውነት ሆኖ ተገኘ።

በአምስት ቀናት ውስጥ ይታለፉ የነበሩ መንገዶች ሰባት ቀናት እንዲወስዱ ድግስ ምክንያት ሆነ። የአፄ ምኒልክን ስም ማንሳትም ሆነ ድምጽን ከፍ አድርጎ እየዘመሩ ለመጓዝ የማያሰጋ ብቻ ሳይሆን የሚያበረታታ ጭምር አጋጣሚ ተፈጠረ።

ለጊዜው ሁሉም ነገር ሰላም መሰለ።

ጉዞ ዓድዋ ከመጀመሩ በፊት በዓድዋ ከተማ የዓድዋ ድል በዓል የሚከበረው በየአምስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ብቻ ነበር።

ጉዞ ዓድዋ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ለተጓዦች አቀባበል በሚል በየዓመቱ የዓድዋ ድል በዓልን ከማክበር አልፎ በወቅቱ የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አስተዳደር የሕዝቡን አንድነትን የሚያጎሉ ሥራዎች መሰራት አለባቸው ባለው መሠረት የዓድዋ ድል በዓል በፌደራል መንግሥት በድምቀት እንዲከበር ወሰነ።

በዚህ ወቅት ጉዞ ዓድዋ ከባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር የ100,000 ብር ድጋፍ ለመጀመሪያ ጊዜ አገኘ። ጉዞ ዓድዋ አራት የተካሄደው 121ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሚከበርበት ወቅት ነበር።

ጉዞውን ለማካሄድ የታቀደውም በ121 ተጓዦች ነበር። ሆኖም በወቅቱ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በየአካባቢው ተፈጥረው የነበሩ ከፍተኛ ውጥረቶች ለመጓዝ ከተመዘገቡት ተጓዦች መሀል ጉዞውን ለማድረግ ፈቅደው የተገኙት ስምንት ተጓዦች ብቻ ነበሩ።

የጉዞ ዓድዋ አራት የመጨረሻ ፍጻሜ በሶሎዳ ተራራ አናት ላይ የተፈጸመ ቢሆንም ከዓመት በፊት ተፈጥሮ በነበረው የተራራ መናድ አደጋ ሳቢያ ወደ ተራራው የሚያስወጡ መንገዶች በሙሉ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ተደረገ።

በዓሉም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከበር በመሆኑ የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በዝግጅቱ ላይ ታድመዋል።

ዝግጅቱም 100ኛው የዓድዋ ድል በዓል ከተከበረ ከ21 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በቀጥታ ስርጭት ተላልፏል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት እንደተለመደው መድረኩ ላይ ደማቅ አቀባበል ከተደረገ በኋላ ተጓዦች መድረክ አግኝተው መልዕክት የሚያስተላልፉበት ዝግጅት መታጠፉን እና በእንግዶች ፊት ተራምደው ብቻ እንዲያልፉ መታዘዙን ለጉዞው አዘጋጆች ተነገራቸው።

በበዓሉ ላይ በቀረበው ተውኔት ውስጥ የዳግማዊ አፄ ምኒልክንም ይሁን የእቴጌ ጣይቱን ስም ካለማንሳት አልፎ መድረክ ላይ ይተላለፉ በነበሩ መልዕክቶች እንዲሁም በየቦታው በተሰቀሉ ግዙፍ ፖስተሮች ላይ አንድም ቦታ ላይ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ስም እንዳይገለጽ መደረጉ የጉዞውን አባላት ሁሉ ያሳዘነ ድርጊት ሆነ።

ተጓዦች ከሕዝቡ ያገኙት ደማቅ አቀባበል ቢያስደስታቸውም መድረኩን አልፈው ወደ ተዘጋጀላቸው አንድ ጥግ ተወትፈው የመድረኩን ዝግጅት መታደም ቀጠሉ።

በዚህም ወቅት የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር የወቅቱ ሚንስትር ዲኤታ የነበሩት ወ/ሮ መዓዛ ገብረ መድኅን ከተቀመጡበት የክብር እንግዶች ወንበር በመነሳት ተወሽቀው ወደ ተቀመጡት ተጓዦች አመሩ።

የእንኳን ሰላም ገባችሁ ደስታቸውን ሁሉንም ተጓዦች እያቀፉ ከገለጹ በኋላ፣ ተጓዦች ስለተከፉበት ምክንያት ሲጠይቁ መድረክ መከልከላቸውን ተናገሩ።

ወ/ሮ መዓዛ ገብረ መድኅን ንዴታቸው ፊታቸው ላይ እየተነበበ በፍጥነት ወደ መጡበት የክብር ወንበር ተመልሰው አዘጋጅ ኮሚቴዎቹ እና ከሚንስትሯ ዶ/ር ሂሩት ጋር ሲነጋገሩ ተጓዦች ከርቀት ሁኔታውን ይመለከቱ ነበር።

መድረክ ላይ ሲተላለፍ የነበረው ሙዚቃ እንደተፈጸመ መድረክ መሪው የጉዞ ዓድዋ ዋና አስተባባሪ ወደ መድረኩ በመውጣት ንግግር እንደሚያደርግ አስተዋውቆ የጉዞውን ዋና አስተባባሪ ወደ መድረክ ጠራ።

የጉዞው አስተባባሪ ንግግሩን እንዲያቀርብ ከተሰጠው 3 ደቂቃ ውስጥ ግማሹን ብቻ በመጠቀም የዳግማዊ አፄ ምኒልክን፣ የእቴጌ ጣይቱን እና የሌሎች አዝማቾችን ስም በመጥራት ጀግኖች አያቶችንን ለመዘከር በመብቃታቸው ተጓዦች ደስተኞች መሆናቸውን በመግለጽ ምስጋና አቅርቦ ወረደ።

በዚያች ዕለት ረዥም ቴአትር እና በርካታ ንግግሮች እንዲሁም ብዙ ዝግጅቶች የተደረጉ ቢሆንም የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ስም በመድረክ የጠሩ ሁለት ሰዎች ብቻ ነበሩ። የጉዞ ዓድዋው አስተባባሪ እና የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ።

በቀጣዩ ዓመት እንደ ባለፈው ዓመት ሁሉ በኦሮሚያ ከተሞች የነበረው አቀባበል የተለየ እና መልካም የነበረ ቢሆንም ወቅቱ ሌላ ችግር ተከስቶ አስፈሪ ድባብ ተፈጥሮ ነበር።

ይኸውም ጉዞው በተጀመረ በ3ኛው ቀን፣ የጥምቀት ቃና ዘገሊላ በዓል ወቅት በወልዲያ ከተማ በተፈጠረ ችግር በርካታ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች ተገድለው ሕዝባዊ ቁጣ ተቀስቅሶ ነበር።

ጉዞው ከተጀመረ ሶስት ቀናት እንዲሁም ወልዲያ ለመድረስ ከ20 በላይ ቀናት የሚቀሩ ቢሆንም በተጓዦች እና ቤተሰቦቻቸው ዘንድ ፍርኅት ማሳደሩ ግን አልቀረም።

የሆነው ሆኖ ጉዞው በተያዘለት መርሐ ግብር ተካሂዶ ከ20 ቀናት በኋላ ተጓዦች ወልዲያን አልፈው ቆቦ ከተማ ድረሱ።

በቆቦ ከተማ ተነስቶ በነበረው አመጽ የበርካታ ህንጻዎች መስታወት ተሰባብረው መኪኖች ተቃጥለው እና በርካታ የንግድ ተቋማት ከጥቅም ውጪ ሆነው ነበር። በዚህ አስፈሪ ኹነት መሐል ማለፍ እና እያንዳንዱን ዝርዝር ታሪክ መጻፍ በዚህ አጭር ማስታወሻ ላይ ማስፈር ከባድ ነው።

ተፈጥሮ የነበረው ሁከት የብሔር ጥላቻ ጎልቶ እንዲወጣ በከፍተኛ ደረጃ ተሠርቶበት የነበረ በመኾኑ ወደ ትግራይ ይሄዱ የነበሩ ተሽከርካሪዎች ይህንን መንገድ መጠቀም አቁመው በአፋር በኩል ይሄዱ እንደነበር ይነገራል። በተጓዦች ግምት መንገድ ዝግ ይሆናል እንጂ ማለፍ እንችላለን ብለው አልገመቱም ነበር።

ጉዞው ቀጥሎ የቆቦ ከተማን በማለፍ ዋጃ ወደ ተባለችው ትንሽዬ ከተማ ተጓዦች እንደደረሱ የነበረው ሁኔታ ሁሉንም ያስደነገጠ ነበር።

የጉዞ ዓድዋ ተጓዦች መስመር ሠርተው በሰልፍ የሚራመዱ በመሆናቸው ከዋጃ በኩል ከፍተኛ ቁጥር ያለው የታጠቀ ሠራዊት እና የጦር ተሽከርካሪዎች የዋጃ ከተማ መግቢያ ላይ ካለ ድልድይ አጠገብ ባልተለመደ መልኩ ካምፕ መስርተው በተጠንቀቅ ቆመው ይጠብቃሉ።

የዋጃ ከተማ መግቢያ ድልድይ ላይ ተጓዦች ሲደርሱ የሁሉም ፍርሀት እየጨመረ የመጣ ቢኾንም ከፊት ለፊት መንገዱን አጥረው የሚታዩ ወታደሮች የተጓዦችን ማንነት መለየት በመቻላቸው ነገሩ ወደ ተረጋጋ መንፈስ ቀስ በቀስ መቀየር ጀመረ።

በወታደሮች ታጅበው ብቅ ያሉት ኮሎኔል እኹት የተባሉ የጊዜያዊ ካምፑ አዛዥ ለተጓዦች ራሳቸውን ካስተዋወቁ በኋላ፣ ሁሉም በሰልፍ እንዲከተሏቸው አዘው ከመንገዱ በስተግራ ወደሚገኝ መታጠፊያ ይዘዋቸው ገቡ። ቦታው በእጅጉ አስፈሪ ነው።

ኮሎኔሉ ከጉዞው አስተባባሪ ጋር መረጃዎችን ከተነጋገሩ በኋላ ጉዞውን ለማድረግ የተፈቀደበትን ደብዳቤ ጠይቀው ተሰጣቸው። ደብዳቤውን አንብበው ከጨረሱ በኋላ በቁጣ መናገር ጀመሩ።

“የፈቀዱላችሁ ሰዎች ምን ነክቷቸው ነው? እንደዚህ አይነት እንግዶች እየመጡ ነው እወቁት ብለው ለእኛ መናገር ነበረባቸው። እናንተ እኮ ከመመታት የተረፋችሁት በተአምር ነው...

“.... ወታደራዊ ሰልፍ ሰርታችሁ ስትመጡ የተደራጀ ጥቃት ሊሰነዝር የሚፈልግ ኃይል የመጣ ኃይል ስለመሰለን ተዘጋጅተን በግራም በቀኝም ቆርጠን ቀለበት ውስጥ ከተናችሁ ነበር። ... ለማንኛውም ተርፋችኋል። በሉ ይህንን ብሉ” አሉና ወታደሮቹ ይዘው የመጡትን የታሸጉ ብስኩቶች ዘረገፉላቸው።

ከቀናት በኋላ የካቲት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. የጉዞ ዓድዋ አምስት አባላት አጉላዕ የተባለችውን ከመቀለ በፊት የምትገኝ ትንሽ ከተማ በመጠኑ እንዳለፉ አንዲት መንገድ ዳር የምትገኝ አነስተኛ ሻይ ቤት በረንዳ ላይ ዙርያ ከበው በመቀመጥ የመጻሕፍት ንባብ ለማከናወን በጋራ ታድመዋል።

ከሻይ ቤቷ ውስጥ አንዲት አስተናጋጅ መጥታ ሽብር የሚመስል መረጃ ለተጓዦቹ አጋራች። “ኃይለማርያም ሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ አቀረበ” የሚል ሰበር ዜና ደጋግሞ በቴሌቪዥን እየታየ ነው ብላ ተናገረች።

ከቤቱ ርቆ ያውም በእግሩ ረዥም ርቀት መንገድ ላይ ለሚገኝ ሰው እንዲህ ያለ ዜና ከፍተኛ መረበሽ የሚፈጥር ነበር። ከደቂቃዎች በፊት መንገዱን ሰንጥቀው ያልፉ የነበሩ መኪኖች እንቅስቃሴ ምን የተለየ ነገር እንደነበረው የታዘበ ሰው አልነበረም።

ቦታው የስልክ ኔትወርክ የሌለበት በመሆኑ በቴሌቪዥኑ ከሚተላለፈው መረጃ በቀር ምን እንደተፈጠረ የሚነግር አንዳችን ፍንጭ አልነበረም።

በዚህም ሳቢያ ቀድሞ 1 ሰዓት ያህል ይፈጅ የነበረው የ6 ኪሎ ሜትር ርቀትን በግማሽ ሰዓት ውስጥ በሩጫ ጭምር ተዋክቦ ወደ ቀጣይዋ ከተማ ሁሉም ከነፈ።

በቅርብ ርቀት የሚገኝ ከተማ ባለመኖሩ የመንገዱን ዳር ተከትሎ የተሠራ አንድ የገጠር ትምህር ቤት በልመና ለማደር ፍቃድ ስለተገኘ ገና ሳይመሽ የዕለቱ ጉዞ ተጠናቆ ተጓዥ ሁሉ በጊዜ ወደ ማደሪያው ተከተተ።

እንዲህ ባለው ሁኔታ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሥልጣናቸው የመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው፤ ፓርቲያቸው ምላሽ እስኪሰጣቸው እና በምትካቸው ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከመሾማቸው በፊት የነበሩት ቀናት ለጉዞ ዓድዋ 5 ተጓዦች ዓድዋ ከተማ እስከሚደርሱበት ቀን ድረስ የፖለቲካው ሁኔታ ያልለየለት በመሆኑ በተጓዦች ላይ ውጥረት ሰንብቶ ከርሟል።

የዚያኑ ዓመት በጉዞ ዓድዋ 5 ፍጻሜ የካቲት 23 ቀን ጉዞ ዓድዋን ለሁለት የሚከፍል አጋጣሚም ተከስቶ ነበር።

***

የቢቢሲ ማስታወሻ፡ ጉዞ አድዋ ከዚህ ቀደም ለዓመታት መከፋፈል ባጠላበት ሁኔታ ሲካሄድ ቆይቷል። "የጥቁር ነፃነት ተምሳሌት"፤ የዓለም ድሃ አገራትን የናቀና ጦር መሳሪያውን የተማመነ ኃይል የተንበረከከበት በሚል የሚዘክሩት ቢኖሩም የአድዋ ታሪክ፣ አተረጓጎም ሐሳባዊ ፍጭቶችንም ማስተናገዱን ቀጥሏል።

አፄ ምኒልክ የነበራቸው ሚና፣ የሰንደቅ አላማ ጉዳይ በታሪክ ተርጓሚዎች ዘንድ መነታረኪያ ሆኖም ቀጥሏል። ለባለፉት ሁለት ዓመታት በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተዛምቶ በመቶ ሺዎችን ሕይወት በቀጠፈው ጦርነት ምክንያት ጉዞው ተገትቶ ቆይቷል።

*ፀሐፊው ያሬድ ሹመቴ ከጉዞ አድዋ አስተባባሪነቱ በተጨማሪ፣ በተለያዩ ፊልሞች በዳይሬክተርነት፣ በፀሐፊነት እንዲሁም ሙዚቃዎችን የሚሰራ ባለሙያ ሲሆን፣ በቅርቡ በቦረና ለተከሰተው ድርቅ ድጋፍ ለማድረግ ገንዘብ በማሰባሰብና በሌሎችም የበጎ ሥራ እንቅስቃሴዎች ይታወቃል።

References

Top Articles
Latest Posts
Article information

Author: Tish Haag

Last Updated: 30/11/2023

Views: 5279

Rating: 4.7 / 5 (67 voted)

Reviews: 90% of readers found this page helpful

Author information

Name: Tish Haag

Birthday: 1999-11-18

Address: 30256 Tara Expressway, Kutchburgh, VT 92892-0078

Phone: +4215847628708

Job: Internal Consulting Engineer

Hobby: Roller skating, Roller skating, Kayaking, Flying, Graffiti, Ghost hunting, scrapbook

Introduction: My name is Tish Haag, I am a excited, delightful, curious, beautiful, agreeable, enchanting, fancy person who loves writing and wants to share my knowledge and understanding with you.